May 15, 2014
ከሮበሌ አባቢያ፤ 14/5/2014
ቅጥረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ
ወያኔ በ1983 አዲስ አበባ ሲገባ እግረ መንገዱን የገበሬውን ልጆች፣ ጋዳፊና የአረብ ሀገር ከበርቴዎች ባስታጠቁት ዘመናዊ ታንክና መሣሪያዎች፣ እያጨደ በሬሳቸውና በደማቸው ላይ እየተረማመደ እንደነበር መሪር የቅርብ ትዝታ ነው። በቅጥረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው ጎጠኛው የወያኔ መንግሥት፣ የኢጣልያ ፋሺስት ያወጣውን በተለይ በአማራና በኦሮሞ ላይ ያነጣጠረውን የከፋፈለህ ግዛው ፖሊሲ ኮርጆ በመከተል፣ የአፄ ምኒልክ ሐውልት እንዲፈርስ ለማደረግ ሕዘቡን አነሳስቶ እንደነበር ይታወቃል።ሆኖም ሙከራው ወያኔ አስቦት በነበረበት ወቅት ባይሳካም፣ ሐውልቱን የማንሳት ሃሳብ አሁንም አለ። ስለዚህ ሕወሐት የሚመራው በውስጡ በሚስጥር በተሰገሰጉ ባንዳዎች እንደሆነ እያደር ሊታወቅ ስለቻለ የእምዬ ምኒልክ ወደጆች መዘናጋት የለባቸውም።
ሐውልቱና ከኢጣልያን ጋር የተደረጉት ሁለት ከባድ ጦርነቶች
እምዬ ምኒልክ፣ እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በገፍ ታጥቆ ኢትዮጵያን ሊወር የመጣውን ጦር፣ አድዋ ላይ ገጥመው ወራሪውን ድባቅ መትተው አንፀባራቂ ድል ሲጎናፀፉ፣ ከሰሜን ሸዋ አብሮአቸው የዘመተው ስምንት ሺህ (8000) ፈረሰኛ የኦሮሞ ሚሊሽያ ሠራዊት በጦርነቱ ለተገኘው ድል ወሳኝ አስተዋፅዖ አድርጎ እንደነበረ በታሪክ የተመዘገበ የጀግንነት ሐቅ ነው። የአድዋው ድል የአውሮፓን ሀያላን መንግሥታትን አስደንግጦ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉአላዊ ነፃ ሀገር እንዲያውቋት አስገድዷቸዋል። ይህ ታላቅ የጥቁር ሕዝብ ድል በዓለማችን ላይ ለሚገኙት ጭቁን ጥቁሮች ሁሉ ሕያው ተስፋ ሰጥቷል።
በሽንፈቷ ሀፍረት የተከናነበችው ኢጣልያ፣ 40 ዓመት ሙሉ በሚስጢር ስትዘጋጅ ቆይታ፦ ሀ) በሚሊሽያዎቻችን ላይ ከሰማይ በአውሮፕላን የቦምብ ናዳ በማዝነብና በዓለም ሕግ የተከለከለውን መርዝ በመርጨት፤ ለ) በምድር በታንክና በመትረየስ የታገዘ መጠነ ሠፊ የሰለጠነ እግረኛ ጦር በማዝመት፤ ሐ) ሕዝቡን በጎሳ ከፋፍላ እርስ በርሱ በማጫረስ፤ መ) አማሮችና ኦሮሞዎች የሥልጣኔ ተፃራሪዎች ስለሆኑ ሌሎች ጎሳዎች በጠላትነት እንዲፈርጇቸው በመስበክ፣ አዲስ አበባን (ሸገርን) እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1936 ዓ.ም ለመቆጣጠር ችላለች። ዋቢ፦ Habešská Odyssea (YeHabesha Jebdu) የሃበሻ ጀብዱ by Adolf Parlesak Translated by Techane Jobre Mekonnen
የፋሺስትን ወረራ ያልተቀበሉት የኢትዮጵያ አርበኞች (በአዲስ አባባና በአካባቢው የሚገኙትን ኦሮሞዎችን ጨምሮ)፣ አራዳ ጊዮርጊስ በዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ዙሪያ ማታ ማታ እየተሰበሰቡ (ሬዲዮ አድማጭ መስለው) ይመካከሩ ነበር። ግራዚያኒ ይህን ሲሰማ ሐውልቱ እንዲነሳና በምሥጢር እንዲቀበር አዘዘ፤ በትእዛዙም መሠረት ሐውልቱ ተነስቶ ሌላ ጋ ተቀበረ። ፋሽስት ኢጣልያ ተሸንፎ ከሀገራችን ሲባረር፣ ሐውልቱ ከተቀበረበት ቦታ ተመልሶ እንደገና በቀድሞ ቦታው ላይ ሊተከል ቻለ።
ጠላት ተገዶ ያከበራቸውን እምዬ ምኒልክን ማክበር የምንኮራበት መብታችን ነው። እምዬ ምኒልክ ሲልቅ፣ የባንዳዎች ውላጅ ወያኔ ሲበሽቅ ሁሌ እደሰታለሁ። ምኒልክ አንድ ያደረጋትን ኢትዮጵያን ወያኔ ሲበታትናት አበክረን መቃወም የውዴታ ግዴታችን ነው። በዚህ ጉዳይ ለሚቃወሙን ተቺዎች መልሳችን ይሄው ነው።
ምኒልክ ከአንኮበር እስከ ሸገር
አፄ ምኒልክ ከአንኮበር ወደ ሸገር ሲመጡ ያጋጠማቸው ተፋላሚ ቱፋ ሙና የተባለ ሐይለኛ የኦሮሞ ገዢ ነበር። አፄው ብልሀተኛ ስለነበሩ አማላጅ ልከው ታረቁና ቱፋ ሙናን ክርስትና አንስተው አበልጅ ሆኑ። የቱፋ ሙና ሰፊ ዘሮች እነ አቶ ብሩ ጎሮንቶ ገፈርሳ ግድብ አካባቢ በስተ ምዕራብ-ደቡብ አንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ይኖሩ ነበር። አቶ ብሩን ባጋጣሚ ሱሉልታ አግኝቻቸው ከተዋወቅን በሗላ፣ ከባለቤቴ ጋር ገፈርሳ ድረስ እየሄድን እንጠይቃቸው ነበር። አቶ ብሩ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ በተገኘበት በታላቅ ሥነሥርዓት ገፈርሳ በምትገኘው ቅድስት ማርያም ቤ/ክ በተፈፀመው ቀብራቸውም ላይ ተገኝቻለሁ።
ምኒልክ ከአንኮበር እስከ ሸገር (አዲሰ አበባ) የመጡት በኦሮሞ ባላባቶች የሚታዳደሩትን ግዛቶች አቋርጠው ነው። ቱፋ ሙና ብቻ ነው በነውጥ የተፋለማቸውና ውጊያው በእርቅ የቆመው። በነገራችን ላይ፣ የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ እኔ አሰከማቀው ድረስ በሸዋ ውስጥ ሰፍኖ የቆየው ባላባታዊ ሥርዓት አራማጆች በአብዛኛው አለጥርጥር የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ።
የተወለድኩት አዲሰ አበባ ቀጨኔ ጋላ ሰፈር በሚባላው መንደር ውስጥ ነው። የከተማውን ዙሪያ ደህና አድርጌ አውቃለሁ። ሸዋ ውስጥ በልጅነቴ በእግሬና በፈረስ ከዚያም ስጎረምስ በመኪና በብዙ አቅጣጫዎች ተዘዋውሪያለሁ። ለምሳሌ፣ ከአዲስ አበባ ተነስተን እስከ 130 ኪሎሜትር ርቀት ዙሪያውን በወፍ በረር ብንቃኝ፣ የክልሉን ባላባትነት የአንበሳውን ድርሻ የኦሮሞ ተወላጆች ይዘውት እንደነበር አያከራክርም ለማለት ይቻላል። አፄ ምኒልክ የመሬት ግብር አስከፈሉ እንጂ የባላባቶችን የመሬት ይዞታ አለምክንያት አልነኩም። ዘውዱንም መሬቱንም እኔ ይዤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ሊቀረው ነው ብለው የመሬት ባለቤትነት በግል የእያንዳንዱ ዜጋ ይዞታ መሆን እንዳለበት በችሎት ላይ ስለመፍረዳቸው በአድናቆት ይነገርላቸዋል።