October 29, 2013
መስፍን አማን
(ከሃርለም፣ኔዘርላንድ)
ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ቅዳሜ ሻይ ቡና ለማለት አምስተርዳም ከወዳጆቼ ጋር በነበረኘ ቀጠሮ ላይ እንደአጋጣሚ ተስፋየም በመሃላችን ተገኝቶ ነበር።የባጥ የቆጡን ስናወራ፣ስለአዲሱ የተፋየ መጽሃፍ አንስቶ የውይይታችንን አቅጣጫ ቀየረው።በመሃሉ ተስፋየ፣ከመጽሃፉ ውስጥ አንዳንድ የማልወዳቸው ምእራፎች ቢኖሩ ትችቶቹን የምቀበል ስለመሆኔ አስረግጦ ጠየቀኝ?።እኔም መጽሃፋን ካነበብኩት በሁዋላ ለጥያቄው መልስ ብሰጥ እንደሚሻል ገልጨለት በዛው ተለያየን። አይደርስ የለም መጽሃፉን ለህዝብ ከመበተኑ በፊት ረቂቁን አነበብኩት። ረቂቁን አንብቤ እንደጨረስኩ ለተስፋየ ጥያቄ መልስ መመለስ እንዳለብ ወሰንኩኝ። ይሁንና በቀድሞው ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ተጽፎ የተሰራጨውን ጽሁፍ መውጣት ተከትሎ በዳያስፖራው አካባቢ አዋራው በመጨሱ ያዘጋጀሁትን ትችት በይደር ለማቆየት ወሰንኩ። በዚህ መሃል ተስፋየ ገብረአብ “የስደተኛው ማሰታወሻ” በማለት ያዘጋጀውን መጽሐፍ ባለፈው ሰሞን በነጻ አሰራጭቶልናል።
ወደ መጽሃፉ ትችት ስመለስ “በደራሲው ማስታወሻ” ውስጥ ያገኘሁት ደራሲ ኢህአዴግን ያገለግል ከነበረው ከቀድሞው ማንነቱ ያልተፋታውን ተስፋየ ገብረአብን ነበር። የእፎይታ መጽሄት ዋና አዘጋጅ እና የቡርቃ ዝምታ ደራሲን የድሮው ተስፋየን በዚህኛው የስነ-ጽሁፍ ስራ ውስጥም ዳግም አገኘሁት።የድሮው ተስፋየ ስል ታዲያ ስነጽሁፍን ለፍቅር፣ለመቻቻል፣እና ለእውቀት ሳይሆን የቆዩና የሻሩ ቁስሎችን መቆስቆሻ፣ያልነበሩትንም በመፍብረክ የእልቂት ነጋሪት መምቻ መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀመውን ማለቴ እንደሆነ አንባቢ እንዲያስተውል
እፈልጋለሁ።”የስደተኛው ማስታወሻ” የነዛ ስራዎች ቀጣይ እንጂ በይዘቱም ሆነ በመልእክቱ ጭብጥ አዲስ የስነ- ጽሁፍ ስራ ነው ለማለት የማያስደፍሩ የብዙ ምእራፎችን አካቶአል። ለዚህ የማቀርበው ምክንያት ሃያስያኑ እንደሚሉት የገጸ-ባህሪ አሳሳሉና የመልእክቱ ጭብጥ አመራረጥ እንዲሁም እንደ ደራሲ በዋነኝነት ማስተላለፍ በፈለገው መልእክት ላይ ነው።