February 27, 2014
ከስንሻው ተገኘ
ወደ ትዝታ ዓለም ወደ ትዝታ ጊዜ በትዝታ ሰረገላ ልወስዳችሁ ነው። እኔ እንኳ በአጻጻፌ አበባዊ ቋንቋ አልወድድም። ለማንኛውም ግን አብረን እንድንነጉድ እጋብዛችኋለሁ። ወደ እንግሊዝ አገር! 1953 እ.አ.አ ወደ አንድ የለንደን ስብሰባ አዳራሽ እንገባለን። እንግዶች የነፃነት ታጋዮች ወደ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት የዌስት ኢንዲስ ተወላጅና የዓለም አቀፍ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ንቅናቄ መሪ የሆነው ጆርጅ ፓድሞን በአዳራሹ ውስጥ ፕሪዚደሙን ለብቻ ይዞታል። የእኔንና የእርስዎን ቡጢ (ጭብጥ) የሚያህል ወፍራሙን ትምባሆ (ቶስካኖ) ጐርሶአል። ጐርናና ድምፁ ሰውንም አዳራሹንም የሚቆጣጠር ዓይነት ነው። ከአፉ የሚወጣው ጢስ በአካባቢው አንዳች ዓይነት ጉም ሠርቶአል። በመካከሉ የሚያሰማው ባለ ግርማ የሆነው ሳሉ ለሰውየው ተጨማሪ ክብር አሸክሞታል።

“ክቡራትና ክቡራን! አዳራሹ ተከፍቶ ንግግር የሚያደርጉት የአፍሪካ ነፃነት ንቅናቄ መሪዎች ወደ ውስጥ ይዝለቁ!” ጆርጅ ፓድሞን ትእዛዝ ሰጠ። አዳራሹ ደግሞ ከግድግዳ እስከ ግድግዳ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቆአል። በአራቱም ማዕዘናት ቄንጠኛ በሆኑ ረዣዥም ሰንደቆች ላይ ወርቃማና ቀለማማ በሆነ መደብ ላይ በጉልህ የሚታዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎች አሉ። ትርኢቱ እንባ ካልጋበዘ ስሕተቱ የኔ ነው። ደካማ ጋዜጠኛ ሰነፍ ጸሐፊ…
አዳራሹ ተከፈተ። የማኦማኦ ንቅናቄ መሪ ወጣት የማይመስሉት ጆሞ ኬንያታ ብቅ አሉ። በደረታቸው ላይ የቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ምስል ያለበት ፒን አድርገዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንደ ሻሽ አድርገው በራሳቸው ላይ ጠምጥመውታል። ቀጥል። የጐልድኮስቱ (በኋላ ጋና) የነፃነት ግንባር መሪ ካዋሚ እንኩሩማህ- ፈርጠም ያለ…ደልደል ያለ..ተክለ ሰውነታቸው ጉልህ የሆነ አርበኛ። ሰንደቅ ዓላማውን በሙሉ ለብሰውታል። የጃንሆይን ምስል ደግሞ በግራ ኮታቸው ክሳድ ላይ ሰክተውታል። ሑፍዌ ቩዋኘ (ኮትዲቮር) ሔስቲንግስ ባንዳ (ማላዊ) ወዘተ ተራ በተራ መጡ። ከመካከላቸው ጐፈር በራሳቸው ላይ ያደረጉ….በእጆቻቸው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ የጃማይካ፣ የደቡባዊ አፍሪካ ታጋዮች ነበሩ። በብዙ ቁጥር። ሁሉም በመንፈስ ኢትዮጵያዊ ነበር። ያ ዘመን ደግሞ በትውልዱ ጃማይካዊ የነበረው ማርከስ ጋርቪ (Black nationalism and Pan-Africanism)ን እንዲሁም የራስ ተፈሪያኒዝምን ፍልስፍና የሚያስፋፋበት ነበር። የሁሉም አገር – ነፃነትዋን ለሺህ ዓመታት አስከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ናት።