April 28, 2014
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
በቅርቡ የሴቶችን ቀን አስመልክቶ በተደረገ የሩጫ ዝግጅት ወቅት የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆችነ ነን ያሉ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶች “አትለያዩን! አትከፋፍሉን! ነፃነት እንሻለን! ለድሃው ይታሰብለት! ኑሮ ከበደን! ውሃ ጠማን! መብራት ናፈቀን!” በማለት በጣም ሰብዓዊና እናታዊ ጥሪ ጮክ ብለው አሰምተው ነበር። ይህም መልካም ድርጊታቸው ለፍትህና ለአንድነት የሚደረግ ህዝባዊ ጥሪ በሚያስበርግጋቸው የወያኔ ባለስልጣናት ሁከት ፈጠራ ተብሎ ተወነጀሉ። ፕሮፌሰር አልማርያም በተቆጣው ብዕራቸው
… ያገሬ ወይዛዝርቶች በምህረት አልባ ጨካኞች ሲንገላቱና ሲወገሩ ከዳር ቆሜ ማየትን ህሊናዬ ፈጽሞ አይፈቅድልኝም። ይልቁንም የእንግልታቸው ምክንያት ሰብዓዊ በሆነው መብታቸው ድምፃቸውን ስላሰሙ በመሆኑ የነሱና የመሰሎቻቸውን ጥሪ በዚህም ሳቢያ የሚደርስባቸውን አበሳ ሁሉ ለአለም አሳውቅ ዘንድ ድምጼን ከፍ አድርጌ እጮሃለሁ…
ብለው ነበር። ከርሳቸው ድምጽ ጋር በማበር የሚያስተጋቡ ድምጾች ይኖሩ ዘንድ እውነት ነውና የኔንም ድርሻ እነሆ እጮሃለሁ። ጩሀቴም ቀደም ሲል በግፍ ለታጎሩ የህሊና እስረኞችና ሰሞኑን ለታፈሱት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች አንዲሁም ለጎበዞቹ የዞን ዘጠኝ የሕዝብ አፈቀላጤዎችም (ብሎገሮችም) ነጻነት ያለኝ ጽኑ ፍላጎት መገለጫ ነው።
ሁከት ማለት የሌሎችን ሰላም ማደፍረስ፥ አምባጓሮና ጸብ ማንሳትና ማነሳሳት፥ የንብረት ጥፋትና በሰዎች ላይ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳትን ማስከተል ነው። እኒህ ወጣት ሴቶች ግን ከዚህ በተቃራኒው የተንገላቱት ሰላም አንዳይደፈርስና ህዝብ እንዳይጎዳ በስልጣን ላይ ያሉት መንግስታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሰላማዊ ጥሪ ነበር ያቀረቡት። የሀሰት ፕሮፖጋንዳው ሰለባ ያልሆነ በሙሉ ወጣቶቹ በአንድነትና በፍትህ የጸናች ሀገር ለመረከብ ከዚህ የበለጠ ቢያደርጉም ተገቢ ነው የሚል ይመስለኛል። የነርሱ አሳሪዎች በነርሱ እድሜ ጠመንጃ አንስተው መጥፎ ነው ብለው የፈረጁትን መንግስት ለመዋጋት ጫካ መግባታቸውን አለመርሳት ብቻ ሳይሆን እንደትልቅ ገድል በየመድረኩና በየመጽሀፉ ሲናገሩና ሲያስነግሩ እንሰማለን። ታዲያ የዛሬው ትውልድ ያውም እንደነሱ ሰው ለመግደል ጠብመንጃ ሳያነሱ ፍትህ አይጉዋደል ብለው በሰላም መጠየቃቸው እንዴት መጥፎ ሁኖ ነው ለእስርና እንግልት የሚዳርጋቸው? ማሰርንና አፈናን እንደ የስልጣን ዘመን ማራዘሚያ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ከሚያስብ አእምሮ ሳይሆን በፍርሃት ከተዋጠና ለውጥ አይቀሬ መሆኑን መቀበል ካቃተው ደካማ ጭንቅላት የሚመጣ ነው። በአንጻሩም ነገ የነርሱ የሆነው ወጣቶች በፍርሀት ተገንዘው አረመኔዎች ሀገራቸውንና ተስፋቸውን ሲያጠፉባቸው በዝምታ ሊያዩ አይቻላቸውም።